Connect with us

News

“ጥያቄው ሌላ መልሱ ሌላ ሆነዋል”- ህወሓት

Kulu Media

Published

on

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለህወሓት የሰጠውን በልዩ ሁኔታ የመመዝገብና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ውሳኔ አስመልክቶ ከህወሓት የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሀምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም የቀረበለትን የተሰረዘውን የህወሓት ህጋዊ ሰውነት ወደ ነበረበት የመመለስ ጥያቄ ተከትሎ በነሓሴ 03 ቀን 2016 ዓ.ም ለህወሓት ”የፖለቲካ ፓርቲዎች በልዩ ሁኔታ ሲመዘገቡ የሚሰጥ የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት” እና ”ህወሓት በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1332/2016 መሰረት በልዩ ሁኔታ የተመዘገበ መሆኑን ስለማሳወቅ” የሚል አርእስት የተሰጠውን በቁጥር አ1162/11/15180 የተፃፈ ህወሓት ስላቀረበው ጥያቄና ቦርዱ የሰጠውን ውሳኔ የያዘ ደብዳቤ ደርሶናል።

በዚህ መሰረት፤ ህወሓት ያቀረበው ጥያቄ በቦርዱ ውሳኔም በግልፅ እንደተቀመጠው ከፕሪቶሪያው ስምምነት፣ ከህግ እና ህወሓት እያደረገ ካለው ተጨባጭ እንቅስቃሴ አንፃር የተሰረዘውን ህጋዊ ሰውነታችን ወደነበረበት እንዲመለስልን የሚል ብቻ ነው። የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ከዚህ በፊት የህወሓት ህጋዊ ሰውነት ወደ ነበረበት ስለመመለስ እና ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ተብሎ በፌደራል መንግስት የቀረበውን አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የሚያሻሽል አዲስ አዋጅ ይዘት አስመልክቶ ውይይት በማድረግ አዋጁ የህወሓትን ህጋዊ ሰውነት እንደማይመልስ በመገንዘብ ከሚመለከታቸው የፌደራል አካላት ጋር ውይይት እንዲደረግ ወስኗል።

TPLF Statement to NEBE

በዚህ መሰረት የህወሓት የስራ ሀላፊዎች ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት የስራ ሀላፊዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማካሄድ የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ መግባባት ላይ ተደርሷል። በአፍሪካ ህብረት ፓነል ውይይትም ይህ ጉዳይ ተነስቶ ህጋዊ ሰውነቱ መመለስ እንዳለበት ስምምነት ተደርሶበታል። ይህንን ተከትሎም ህወሓት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ሰውነቱን ወደነበረበት እንዲመለስለት ብቻ በሀምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ጥያቄ አቅርቧል።

ከዚህ የተነሳም ‘ጥያቄው ሌላ መልሱ ሌላ’ ሆነዋል።

ሆኖም ቦርዱ የፕሪቶሪያውን ስምምነት፣ ከዚህ በፊት በሌሎች የፌደራል ተቋማት የተሰጡትን ውሳኔዎች፣ ሌሎች ህጎች እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረሱ መግባባቶች ወደጎን በመተው ጥያቄውን ”በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ” መልሷል። ከዚህ የተነሳም ‘ጥያቄው ሌላ መልሱ ሌላ’ ሆነዋል።

የፍትህ ሚኒስቴሩ ደብዳቤ ከህወሓት እውቅና ውጪ የተፃፈ ነው

ከዚህ ባሻገር፤ 1) ምንም እንኳን ቦርዱ የህወሓት ጥያቄ ህጋዊ ሰውነት መመለስ ብቻ እንደሆነ በግልፅ ያስቀመጠ ቢሆንም ከህወሓት ጥያቄ እና እውቅና ውጪ በፍትህ ሚኒስቴር የተፃፈውን ደብዳቤ በአባሪነትና መነሻነት ጠቅሷል። 2) ህወሓት ባቀረበው ማመልከቻ ላይ በማሻሻያ አዋጁ አንቀፅ (2) ላይ የተቀመጡትን መቅረብ አለባቸው ተብለው የተቀመጡትን ዝርዝሮች በማሻሻያ አዋጁ መሰረት እንደቀረቡ ገልጿል። ሆኖም የፍትህ ሚኒስቴሩ ደብዳቤ ከፍ ብሎም እንደተገለፀው በህወሓት በኩል ምንም ዐይነት ጥያቄ ሳይቀርብና ከህወሓት እውቅና ውጪ የተፃፈ ነው። በይዘቱም ህወሓት አይስማማም። በህወሓት የቀረበውን ማመልከቻ እና አባሪዎቹ የሚመለከትም ህወሓት የተሰረዘውን ህጋዊ ሰውነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ የሚያግዙ ሰነዶች ማለትም የፓርቲው ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ እና የጠቅላላ አመራሮቹ ዝርዝር የያዘ ሰነድ እንጅ በማሻሻያ አዋጁ መሰረት እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዐንቀፅ 2(14) መሰረት የስራ አስፈፃሚ አባላት ስም፣ አድራሻ እና በተለየ ሁኔታ ሀላፊነት ወስደው ቃል የሚገቡበትን የተፈረመ ሰነድ ለቦርዱ አላቀረበም።

በነበረው ሂደት ቦርዱ በአዲሱ ማሻሻያ ህግ መንፈስ የራሱ ፎርም አዘጋጅቶ የህወሓት ስራ አስፈፃሚ አባላት ስም፣ ፌርማ፣ አድራሻ ሞልተው ሀላፊት ወስደው እንደሚሰሩ የሚገልፅ ሰነድ እንዲቀርብለት ጠይቆ በህወሓት በኩል ከማመልከቻው የሚጣጣም ሰነድ ካልሆነ በስተቀር በአዲሱ ህግ ወይም ቦርዱ ባቀረበው ፎርም መሰረት የተለየ ሀላፊነት ወስዶ የሚፈርምበት ምክንያት እንደሌለ ገልፆ ሳይስማማ በመቅረቱ ቦርዱ በቀረበለት ማመልከቻ ብቻ ውሳኔውን እንደሰጠ ይታወቃል።

የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ…

በአጠቃላይ በቦርዱ ውሳኔ ላይ የተካተቱት ዝርዝር ይዘቶች አዲስ በወጣው ማሻሻያ ህግ መሰረት የተቀመጡና ህወሓት ካቀረበው ጥያቄ ጋር የማይገናኙ ናቸው። ስለሆነም ምንም እንኳን ቦርዱ ህወሓት በልዩ ሁኔታ ተመዝግቧል ቢልም ውሳኔው በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1332/2016 መሰረት በልዩ ሁኔታ የተመዘገበ መሆኑን ገልጿል። ስለሆነም ድርጅታችን ህጋዊ ሰውነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ያቀረበውን ጥያቄ የማይመልስ በመሆኑ አልተቀበለውም። ውሳኔው በፕሪቶሪያው ስምምነት ያልተመሰረተ፣ ከዚህ በፊት በሌሎች የፌደራል ተቋማት የተሰጡትን ውሳኔዎች እንዲሁም የነበሩ ውይይቶችን የሚቃረኑ ዝርዝር ይዘቶች በህወሓት ላይ የሚጭን በመሆኑ የቀረበውን ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ ህወሓት የፓርቲው ሕገ ደንብ በሚፈቅድለት መልኩ ተያያዥ ስራዎች ያከናውናል። የፌደራል መንግስቱም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ ያቀርባል።

ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለሰማእታት!


Discover more from Kulu Media ኩሉ ሚድያ

Subscribe to get the latest posts sent to your email.

Discover more from Kulu Media ኩሉ ሚድያ

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading